@Abyssinia today

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ቦይንግ 777 አውሮፕላኖችን ሊገዛ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አራት ቦይንግ 777 ለመግዛት ተስማማ። አየር መንገዱ የአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ሲሆን፥ መቀመጫውን ቺካጎ ካደረገው የቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር ቦይንግ 777 ኤከስን ለመግዛት እየተነጋገረ ይገኛል። ስምምነት ከተደረሰባቸው አራት አውሮፕላኖች መካከል ሁለቱ፥ ባለፈው ሰኔ ወር በፓሪስ በተደረገው የአየር ትራንስፖርት አውደ ርዕይ ስምምነት የተደረገባቸው መሆኑ ተነግሯል። ከዚህ በተጨማሪ 777 ኤክስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት እየተደራደርን ነው ያሉት፥ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ናቸው። አሁን ለመግዛት የተስማማናቸው አውሮፕላኖች አቅማችንን ለማሳደግ እንጅ፥ ሌሎች አውሮፕላኖችን ለመተካት አይደለም ነው ብለዋል። አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን በ2018/2019 እንደሚረከብ ተጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ላይ የሚገኙ ስድስት 777 ኤፍ የጭነት አውሮፕላኖች አሉት። ምንጭ፦www.flightglobal.com

በሲሚንቶ እጥረት የበርካቶቹ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቆሟል-የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች የሲሚንቶ እጥረትና የክፍያ መዘግየት ምክንያት በርካታ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መቆሙን አሰተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ተናገሩ። ብዙሃኑ ስራ ተቋራጮች ሰራተኞቻቸውን እስከመበተን ደርሰዋል። ችግሮች እየተደራረቡበት ያለው የ20/80 የቤት ልማት መርሃ ግብር በተያዘለት ፍጥነት መጓዝ እንዳልቻለ የበርካቶች ትዝብት ነው። ከሰሞኑ ሰፈራ አራብሳ ወደ ተባለ የአዲስ አበባ አካባቢ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘጋቢ አምርቶ ነበር። በዚህ አካባቢ ዓመታትን ያስቆጠሩ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታዎች በጅምር ላይ ባሉበት እንደሚገኙ ታዝቧል። ግንባታዎቹ በየካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስር ያሉ ሲሆኑ፥ ፅህፈት ቤቱ 61 የስራ ተቋራጮችን ይዞ 140 ህንፃዎችን እየገነባ ቢገኝም የህንፃዎች ግንባታ ግን በችግር ተተብትቦ ተይዟል። በዚህ ችግር ምክንያትም አንዳንዶቹ ግንባታዎች አራት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፥ የተቀሩት ደግሞ ከሁለት ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ወስደው ከአንድና ሁለት ፎቅ በላይ መደርደር አቅቷቸው እንደቆሙ ናቸው። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አማካሪና ስራ ተቋራጮች ለዚህ ጉድለት በርካታ ችግሮችን ያቀረቡ ሲሆን፥ የዚህ ግንባታ ፕሮጀክት ዋነኛው ማነቆ ግን የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ነው፤ ሲሚንቶ በዚህ የግንባታ መንደር ውስጥ አሁን ላይ የለም ማለት ይቻላል ይላሉ። በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት በርካታ ስራ ተቋራጮች መስራት የሚገባቸውን ስራ እየሰሩ አይደሉም፤ ሰራተኞቻቸውንም እንደበተኑ የተናገሩ ስራ ተቋራጮች አሉ። የሲሚንቶ እጥረቱ ግንባታውን ብቻ ሳይሆን ያስቆመው እንደ ፕሪካስትና ብሎኬት ያሉ የግንባታ ግብዓትች ላይም አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል። ስራ ተቋራጮቹ እና አማካሪዎቹ ይህን ችግር በተመለከተ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፥ ችግሩ ተፈቷል ከማለት በዘለለ በተጨባጭ መልስ ማግኘት እንዳልቻሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የየካ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መለስ ተገኘ እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች አሁንም ምላሻቸው ችግሮቹ እየተፈቱ ነው የሚል ሆኗል። በእርግጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ችግሮችን እንዳለፉ ስራ አስኪያጁ አቶ መለስ ይናገራሉ። ለአብነት የፕሪካስት ምርት እጥረት አጋጥሞ ነበር፤ እጥረቱ እንዲከሰት ምክንያት የሆነው ደግሞ ከግንባታ አካባቢው ውጪ ባሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማህበራት በአግባቡ ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ ባለማቻላቸው ውላቸው እንዲቋረጥ በመደረጉ ነው። ውላቸው ሲቋረጥ እነሱን የሚተኩ ማህበራት ባለመኖራቸው ለወራት ያህል የፕሪካስት ምርት አቅርቦት ችግር ነበር። አሁን ግን ወደ 10 የሚጠጉ ማህበራት ገብተው እየሰሩ ስለሚገኙ የፕሪካስት ምርት ችግር የለም ይላሉ አቶ መለስ። የስላቭ ብሉኬት እና የግድግዳ ብሉኬት የአቅርቦት ችግር የለም የሚሉት አቶ መለስ፥ አሁን ላይ ዋነኛ ችግር የሆነው የሲሚንቶ አቅርቦት ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል። አሁን ፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ እያደረገ ያለው በመጠን ያነሰውን የሲሚንቶ አቀርቦት እየሰጠ የሚገኘው ፕሪካስት፣ ብሎኬት እና ስላቭ ብሎኬት ለሚያመርቱ ማህበራት ነው። ስራ ተቋራጮች ግን የሲሚንቶ ግብዓት የማይሰጣቸው ሲሆን፥ የሲሚንቶ እጥረቱ የከፋ መሆኑን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘጋቢ በመኖሪያ መንደር ግንባታ አካባቢዎች ባደረገው ቆይታ ተመልክቷል። የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ በበዙበት ሃገር በቤት ልማት መርሃ ግብር ላይ እንዴት የሲሚንቶ ግብዓት እጥረት ይነሳል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ይህ የሲሚንቶ እጥረት ደግሞ የአንድ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ችግር ብቻ ሳይሆን፥ መጠኑ ቢለያይም በ18 የከተማዋ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቶች ላይ የሚስተዋል ነው። ከዚህ ቀደም የግንባታ ግብዓቶችን ገዝቶ የሚያቀርበው ራሱ የከተማዋ ቤቶች ልማት ፕሮጀከት ጽህፈት ቤት ነበር። አሁን ግን የፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱን የግዥ ስራዓት ለማስተካከል ሲባል በከተማዋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በኩል ሁሉም የግንባታ ግብዓቶች ተገዝተው ነው የሚቀርቡለት። የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀከት ፅህፈት ቤት ለሲሚንቶ እጥረት የመዳረጉ ምክንያትም፥ ከዚህ እንደሚመነጭ የፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሓረጎት ዓለሙ ይናገራሉ። ጨረታ አውጥቶ አወዳድሮ አሸናፊው እስኪታወቅ ድረስ ረጅም ጊዜ መውሰዱ ለዚህ ችግር ዳርጎናል ነው ያሉት አቶ ሓረጎት በእርግጥ ይህን እጥረት ለማቃለል ጊዚያዊ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል እስከ 200 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ፥ ከሙገር በቀጥታ ፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ግዥ በመፈፀም ችግሩን ለማስታገስ ቢሞከርም ፍላጎቱን አላረካም። የከተማዋ የመንግስት ግዥ አስተዳደር በጨረታ አሸናፊ ናቸው ያላቸውን የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎችን በመለየቱ፥ ከዚህ በኋላ ሲሚንቶ ችግር የሚሆንበት ሁኔታ አይኖርም ባይ ናቸው። የስራ ተቋራጮች ግን የሲሚንቶ ችግር ቢፈታም ሌላም ችግር መኖሩን በመጥቀስ፥ ለሰራነው ስራ ሊፈፀምልን የሚገባው ክፍያ በመዘግየቱ በስራችን ላይ ጫና እያሳደረብን ነው ብለዋል። አቶ ሓረጎት ክፍያን በተመለከተ የፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ችግር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተንዛዛ የክፍያ ስርዓት የሚከተል በመሆኑ ከዚህ የመጣ ችግር ነው ሲሉ ችግሩን ከፅህፈት ቤታቸው አርቀውታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ጣቢያችን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ ሃላፊዎችን አግኝቶ ለማናገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። ፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ግን ከእነ ችግሮቹም ቢሆን እየገነባቸው ያሉትን የመኖሪያ ቤቶች፥ በተያዘው ዓመት ግንባታቸውን ሰማኒያ በመቶ ለማድረስ እቀዶ እየተጓዘ ነው። በታደሰ ብዙዓለም

ደቡብ ሱዳን የምግብ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የቀረበባትን ውንጀላ አጣጣለች ደቡብ ሱዳን የምግብ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የቀረበባትን ውንጀላ አጣጥላለች። ሀገሪቱ በሰሜናዊ የወው እና የባህረ ኤል ጋዛል ክልሎች ሆን ብላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲራቡ በማድረግ ምግብን እንደጦር መሳሪያ ተጠቅማበታለች የሚለው ውንጀላ ሀሰት ነው የሚል ማስተባበያ ሰጥታለች። የፕሬዚዳንት ኪር ቃል አቀባይ አቴኒ ዌክ አቴኒ እንደተናገሩት፥ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የደቡብ ሱዳን የማዕቀብ ኮሚቴ የደረሰው ሪፖርት መሰረተ ቢስ ነው። የሀገሪቱ መንግስት በክልሎቹ ሰብዓዊ ድጋፎች በፍጥነት እንዲደርሱ እያደረገ ያለውን ጥረት ከግምት ያላስገባ ሪፖርት መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት። የደቡብ ሱዳንን ህዝቦች መንግስት ሊያስተዳድራቸው የሚፈልግ በመሆኑ ሆን ተብሎ የሚቀርብላቸውን ምግብ በማቋረጥ እንዲራቡ አልተደረገም ነው ያሉት። በቅርቡ የወጣው የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት በወው አካባቢ የሚደርሱ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በመከልከል በርካታ ሰዎች ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡና በርሃብ ምክንያት እንዲሞቱ ተደርጓል የሚል ነው። ሆኖም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ባሳለፍነው ሳምንት የፀጥታ ሃይሎች በግጭት አካባቢዎች የሚደርሱ ሰበዓዊ እርዳታዎችን እንዳያስተጓጉሉ አዘዋል። በዚህም ርሃብ ለተጋረጠባቸው የግጭት አካባቢዎች የምግብ እርዳታዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ ፈቅደዋል።

ፎርድ በእንቅልፍ ምክንያት የሚደርስ የተሽከርካሪ አደጋን የሚቀንስ ኮፍያ ሰራ ፎርድ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ በእንቅልፍ ምክንያት የሚደርስ የተሽከርካሪ አደጋን የሚቀንስ አዲስ ኮፍያ መስራቱን አስታውቋል። ከተሽከርካሪ አደጋ መንስኤዎች ውስጥ አሽከርካሪዎች መኪና በመንዳት ላይ እያሉ የማንቀላፋት ወይም በእንቅልፍ መያዝ አንዱ ነው። በተለይም እንዲህ አይነቱ ችግር ከባድ ተሽከርካሪዎችን በሚያሽከረክሩ ሹፌሮች ላይ በስፋት የሚስተዋል ሲሆን፥ ምክንያቱ ደግሞ ነጻ የሆነ መንገድ ላይ ለረጅም ሰዓት ያለ እረፍት ስለሚያሽከረክሩ ነው። ታዲያ ፎርድ ኩባንያ ለዚህ መፍትሄ ይሆናል ያለውን አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ ያለ ሲሆን፥ ይህም አሽከርካሪዎች በእንቅልፍ ስሜት ውስጥ ሆነው በሚነዱበት ጊዜ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው። ኮፍያው የመቆጣጠሪያ ስርዓት የተገጠመለት ሲሆን፥ አሽከርካሪው በማሽከርከር ላይ እያለ በሚያንቀላፋበት ጊዜ ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት አሸክርካሪው መኪናውን አቁሞ እረፍት እንዲወስድ ለማድረግ የሚረዳ ነው። ኮፍያው በፎርድ ኩባንያ ስር በሚገኘው የብራዚል የከባድ መኪናዎች ማምረቻ ፋብሪካ የተሰራ ሲሆን፥ ሰዎች ለመደበኛ አገልግሎት ከሚያደርጉት ኮፍያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ሆኖም ግን ሰዎች በእንቅልፍ ውስጥ ሆነው መኪና እንዳያሽከረክሩ የሚረዳ መከተተያ እና መቆጣጠሪያ ቁሶች ተገጥመውለታል። አሽከርካሪዎች መኪናቸውን በማሽከርከር ላይ እያሉ የእንቅፍል ስሜት በሚጫናቸው ጊዜ ኮፍያው እንዲነቁ አሊያም አቁመው እረፍት እንዲወስዱ የሚረዳ ሶስት አይነት ምልክቶችን እንደሚያሳያቸውም ተነግሯል። ምልክቶቹም ንዝረት፣ ድምፅ ማሰማት እና የመብራት ምልክት መስጠት ናቸው። ፎርድ የኮፍያውን ውጤታማነት ለማረጋገጥም ለ8 ወራት ያክል በተመረጡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ ሙከራ ማድረጉም ተነግሯል። ሆኖም ግን ኮፍያው መቼ ለገበያ ይቀርባል በሚለው ዙሪያ ፎርድ የረጅምም ይሁን የአጭር ጊዜ እቅዱን በይፋ አላሳወቀም ነው የተባለው። ምንጭ፦ www.cnet.com (http://www.cnet.com/)

አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚነት ሲወዳደሩ የቆዩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ። አቶ ተክለወይኒ ዛሬ በመቐለ ከተማ በሰጡት መግለጫ፥ “ባለፈው ዓርብ እለት የተናገርኩት ንግግር ትክክል አልነበረም” በማለት በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ንግግራቸውም የጉባኤው ተሳታፊዎች ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉትን የመቐለ ከተማና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ክለቦችን እንዲሁም የመቐለ ስታዲየምን እንዲጎበኙ ከማሰብ የመነጨ ነው ብለዋል። በመግለጫቸው ያደረጉት ንግግር ትክክል ባለመሆኑ ይቅርታ እጠይቃለሁ ነው ያሉት። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን እና ሴቶችን በተለይም የመቐለ ከተማ ሴቶችንም ይቅርታ ጠይቀዋል። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚነት፥ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትን በመወከል ሲደረግ በነረበረው ምርጫ ውክልናቸው መነሳቱንም ተቀብለዋል። አቶ ተክለወይኒ በቀጣይ ጊዜያት ከእግር ኳሱ እንደማይርቁም በዛሬው መግለጫ ተናግረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን በተመለከተ በነገው እለት መግለጫ እንደሚሰጥ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።

አሜሪካ በዋዮሚንግ የሚገኘው የሚሳኤል ጣቢያዋ ላይ በ5 ቢሊየን ዶላር ማሻሻያ ልታደርግ ነው የአሜሪካ መንግስት በዋዮሚንግ ግዛት የሚገኘውን የኒኩሌር ሚሳኤል ስርዓት ላይ በ5 ቢሊየን ዶላር ማሻሻያ ሊያደርግበት መሆኑ ተነግሯል። ማሻሻያውም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦርን የማዘመን ስራ አካል መሆኑም ተነግሯል። የአሜሪካ ጦርም ለማሻሻያው የተበጀተውን ገንዘብ በወዮሚንግ ኤፍ.ኢ ዋሬን አየር ሀይል ማዘዣ ጣቢያ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤል ስርዓትን ለማዘመን ነው የሚጠቀምበት ተብሏል። በዋዮሚንግ ስቴት የሚገኘው ኤፍ.ኢ ዋሬን አየር ሀይል ማዘዣ ጣቢያ አሜሪካ ካላት ሶስት ስትራቴጂክ ማዘዣ ጣቢያዎች አንዱ ነው። ማዘዣ ጣቢያው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1867 የተቋቋመ ሲሆን፥ ሚኒትማን 3 የተባሉ 150 አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች አሉበት። አሁን በተበጀተው ገንዘብ የሚደረገው ማሻሻያም አዳዲስ የሚሳኤል መገንባትን ጨምሮ፤ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎችን አቅም ማሳደግ የሚችል የኔትዎርክ ማሻሻያ ስራዎችም ይሰራሉ። ሚኒትማን የተባለው ሚሳኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1961 የመጀመሪያ ሙከራ የተካሄደበት ሲሆን፥ እስከ ሶስት የሚደርስ የኒኩሌር አረሮችን መያዝ ይችላል። ሚሳኤሉም እስክ 13 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በመወንጨፍ ኢላማውን መምታት የሚችል መሆኑም ተነግሯል። የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርም አዲስ የኒኩሌር የጦር መሳሪያ ፖሊሲ ላይ እየሰራ ነው የተባለ ሲሆን፥ ይህም ዋሽንግተን የኒኩሌር አቅሟን እንድታሳድግ የሚያግዛት ነው። አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ 450 የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች ባለቤት እንደሆነችም መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል።

Iraq-Iran earthquake: Deadly tremor hits border region በኢራቅና በኢራን በደረሰ ርዕደ መሬት ከ135 በላይ ሰዎች ህይወት አለፈ በኢራቅ እና በኢራን ድንበር አቅራቢያዎች በደረሰ ርዕደ መሬት በትንሹ የ135 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል። በሬክተር ስኬል መለኪያ 7 ነጥብ 3 ማግኒቲዩድ ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬቱ በኢራቅ እና ኢራን በሰሜናዊ ድንበር አካባቢ ነው የተከሰተው። በምእራብ ኢራን ኬርማንሻህ ግዛት በተከሰተው ርእደ መሬት በትንሹ የ129 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው የአካባቢው ባለስልጣናት ለኢራን መገናኛ ብዙሃን የገለጹት። ከዚህ በተጨማሪም በኢራቅ የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉም ተገልጿል። በእዛኛዎቹ ተጎጂዎች ከድንበር 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የኢራኗ ሳርፖል ዘሃብ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውም ተነግሯል። የከተማዋ ዋና ሆስፒታልም በርእደ መሬቱ ጉዳት ስለደረሰበት ተጎጂዎችን የመርዳት ስራን አስቸጋሪ እንዳደረገው ነው የተነገረው። የኢራን የቀይ ጨረቃ ድርጅት ሃላፊ ሞርቴዛ ሳሊም እንደተናገሩት፥ ርእደ መሬቱ በስምንት ገጠራማ አካባቢዎችም ተከስቷል። በዚህም የተነሳ የተወሰኑ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሀይል እና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የተቋረጠባቸው መሆኑንም ገልፀዋል። በኢራቅ በኩል ደግሞ ከፍተኛው ጉዳት የደረሰው በዳርባንዲካሃን ከተማ ሲሆን፥ ከተማዋ የኩርዲስታን ከተማ ከሆነችው ሱላይማኒያህ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። በአካባቢው ያለው ሁኔታም አስጊ መሆኑ ነው እየተነገረ ያለው። የርዕደ መሬቱ ንዝረትም እስከ እስራኤል፣ ቱርክ እና ኩዌት ድረስ ዘልቆ መሰማቱም ተነግሯል። ምንጭ፦ www.bbc.com (http://www.bbc.com)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኳታር ናቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኳታር ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዶሃ የደረሱ ሲሆን፥ በቆይታቸውም ከኳታሩ ኤሚር ጋር እንደሚወያዩ ተነግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ በሚናሮቻው ቆይታም የሁለቱን ሀገራት በሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት እና የጋራ ጥቅም ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል። የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒሲትር ኃይለማርያም ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ እና ፖለቲካዊ ትስስር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታሰዋል። በኤሚሩ የኢትዮጵያ ጉብኝት ወቅትም ሁለቱ ሀገራት መካከል በንግድ፣ ኢኮኖሚ እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ተደርሶ ነበር። ምንጭ፦ www.gulf-times.com (http://www.gulf-times.com)

7ኛው የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ!የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች 7ኛውን የጋራ ስብሰባ በግብፅ ካይሮ አካሂደዋል። ስበሰባው ከህዳር 2 እስከ ህዳር 3 2010 ዓ.ም በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ መካሄዱን የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በካይሮ የተካሄደው ስብሰባም ቀደም ሲል ጥቅምት 8 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተካሄደው የቀጠለ ሲሆን፥ ባልተቋጩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ እና ጉዳዮቹን ለመቋጨት ያለመ ነበር። እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፥ “ምንም እንኳን በጉዳዩ ላይ ስምምነት ለመድረስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል”። ግብፅ በማማከር አገልግሎት ውሉ መሰረት ረቂቅ የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርቱ እንዲስተካከል እና የሶስቱ ሀገሮች አስተያየቶች ለአማካሪ ድርጅቱ እንዲላኩ የተደረገውን ጥረት በተደጋጋሚ በመቃወሟን የገለፀው ሚኒስቴሩ፥ በዚህም ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም ብሏል። በመሆኑም ይህ የግብፅ አካሄድ ለጥናቶቹ መዘግየት አብይ ምክንያት መሆኑንም በመግለጫው አንስቷል። ምንም እንኳን በካይሮው ስብሰባ ጉዳዩን መቋጨት ባይቻልም፤ የሶስቱ ሀገሮች የውሃ ሚኒስትሮች በወደፊት አቅጣጫዎች ዙሪያ ለመወያየትና እና ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው። የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና የግብጽ የውሀ ሚኒስትሮች ጥቅምት 8 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስብሰባ ማድረጋቸው ይታወሳል። ስብሰባውም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን የሚያጠኑ ሁለት ኩባንያዎችና የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚመሩበትን ረቂቅ መመሪያ በማዘጋጀት ነበር የተጠናቀቀው። የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የሱዳኑ አቻቸው ሙአተዝ ሙሳ እና የግብጹ ውሃ ሃብትና መስኖ ሚኒስትሩ መሃመድ አብደል አቲ የህዳሴውን ግድብ መጎብኘታቸውም ይታወሳል።

Warning: preg_match(): Compilation failed: invalid range in character class at offset 12 in /customers/9/f/8/abyssiniabroadcastingcorporation.com/httpd.www/wp-content/plugins/js_composer/include/classes/shortcodes/vc-basic-grid.php on line 171